ጥራት ያለዉ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የሙያ ማህበራት ትልቅ ድርሻ አላቸው” የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ

የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ፌሎሺፕ የተጀመረበትን 10ኛ ዓመት አክብሯል። በአከባበር ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ እንደተናገሩት መንግስት ጥራት ያለዉ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የሙያ ማህበራት የማይተካ ሚና እንዳላቸዉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ አመራሮችና ባለሙያዎች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በኮቪድ 19 ወርሽኝ ወቅት ከመንግስት ጎን በመቆም የዜጎቻችንን ጤና ከመጠበቅ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸዉን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዉ ሶሳይቲዉ የቲቢ በሽታ መከላከልና መቆጣጣር፣ የካንሰር ህክምና እና ሌሎች የጤና ፕሮግራሞች ላይ መመሪያዎችና ስትራቴጅዎችን በመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪም ከኢስት አፍሪካ ትሬይኒንግ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በዘረጋው የፌሎውሺፕ ፕሮግራም 19 ሀኪሞች በመስኩ እንዲመረቁ ማድረጉም የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለፕሮግራሙ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ምስጋናና እዉቅና ተበርክቶላቸዋል።

ሁሉም የጤና ሙያ ማህበራት መንግስት ጥራት ያለዉ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ያለዉን ስራ ከመደገፍ አንጻር እያደረጉ ያሉትን ጥረት አጠናክረዉ እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አንዱአለም ደነቀ፣ የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ፕሬዚደንት እና የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ራሄል አርጋውን ጨምሮ የሶሳይቲው አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝቷል።

Previous slide
Next slide